ይህ የተገለፀው ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሽን ባንክ ጋር በአጋርነት የቴሌብር የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ሐምሌ 29ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል በተደረገው የመክፈቻ ዝግጅት፤ ፐርፐዝብላክን ወክለው የተገኙት ዋና ድጋፍ ሰጪ ቢሮ ሀላፌ ወ/ሮ ሶፍያ ነጋሽ በተለይ ለፐርፐዝ ብላክ ሚዲያ እንደተናገሩት፤ ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሽን ባንክ ጋር በአጋርነት የቴሌብር የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ማስጀመሩ ፐርፐዝብላክ ከሰነቀው ራዕይ ጋር የሚሄድ በመሆኑ ያስደስታል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሶፍያ ነጋሽ አክለውም ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ለሀገራችን ፈር ቀዳጅና ሰፊውን የማህበረሰባችንን ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ በመሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ታሪክ ለማድረግ የጀመርነውን ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
በዚህ ረገድ የዲጂታል ኢትዮጵያን ራዕይ እውን ከሚያደርገው ኢቲዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ በመስራት ሰፊውን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ የበኩላችንን አስተዋፅኦ እናበረክታለን በማለት ገልፀዋል፡፡
ሌላው ከፐርፐዝብላክ ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሪቴል ዲቪዥን ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ ጌታችው፤ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ አጋር ሆኖ ጉሊት ከሚሸጡ ከገበሬው ምርት አከፋፋይ ሴቶች እና ከገበሬው ምርት አከፋፋይ ወጣቶች ጋር የጀመረውን ሥራ ተግባራዊ ለማድረግ ኢቲዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር አማካኝነት ዘመናዊ የፋይናስ አገልግሎት አሰራርን እና የፋይናንስ መሰረተ ልማትን መዘርጋቱ ለስራችን መሳካት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፤ በመሆኑም ፐርፐዝብላክ ስራ ያስጀመራቸው ጉሊት የሚሸጡ ምርት አከፋፋይ ሴቶች የቴሌብር አካውንት እንደሚከፍቱና ለደንበኞቻችው በቴሌ ብር ሽያጭ እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
አያይዘውም ቀደም ሲልም ኩባንያችን የአክሲዮን ሽያጩን በቴሌብር መተግበሪያ እና በአጭር ቁጥር *127# ላይ በመደወል የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች አክሲዮንን መግዛት የሚችሉበትን አማራጭ ይፋ በማድረጋቸን በርካቶች ከ1ሺህ ብር ጀምሮ አክሲዮን በመግዛት አባል እየሆኑ በመሆኑ ይህንን የግብይት ሥርዓት የዘረጋው ኢትዮ ቴሌኮም ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል፡፡
ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ በአዲስ አበባ ከተማ የከፈታቸው የከገበሬው መደብሮች ደንበኞች በቴሌ ብር ክፍያ መፈፀም የሚችሉበትን አገልግሎት መጀመራቸው ይታወቃል።
ቴሌብር የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት ለማህበረሰባችን በተለይም በዋናነት መደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ላልሆነው የማህበረሰብ ክፍል ሁለንተናዊ ለውጥና መሻሻል ከፍተኛ ሚና ያላቸውን፣ እንዲሁም የፋይናንስ አገልግሎት ከማግኘት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የኦቨርድራፍትና የቁጠባ አገልግሎቶችን ከዳሽን ባንክ ጋር በአጋርነት መስጠት እንዲችል ከብሔራዊ ባንክ በተሰጠው ፈቃድ መሰረት አገልግሎቱን ሐምሌ 29 ቀን 2014 ዓ.ም አስጀምሯል።
የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥና ለህዝባችን ተጨማሪ እና ከፍተኛ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር አገልግሎትን ለማቅረብ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የዘረጋውን መጠነ ሰፊ መሠረተ ልማት በመጠቀም በግንቦት 03 ቀን 2013 ዓ.ም “ቴሌብር” የተሰኘውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።
በዋሲሁን ዋጋው
Leave a Reply