ኤም ኤስ ኤ የተሰኘ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ከፐርፐዝብላክ ኢቲ ኤች የግብርና ምርቶችን ለመውሰድ 3.5 ቢሊዮን ብር ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ የተፈረመው ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች 1ኛ አመት የምስረታ በዓሉን ባከበረበት ወቅት ነው። ድርጅቱ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር 3.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የግብርና ውጤቶች እንዲያቀበርብለት መሆኑም ተነግሯል። ክብረ በዓሉ እኔም ገበሬ ነኝ በሚል መሪ ቃል በፐርፐዝብላክ ዋና መስሪያ ቤት የተከወነ ሲሆን የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ከ 250 በላይ ተጋባዝ እንግዶች በተገኙበት ጫፍ እስከ ጫፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች የሚመግበው አርሶ አደር ሲከበርና ሲሞገስ አምሽቷል ፡፡መርሃግብሩ በብሔር ብሄረሰቦች ጥዑመ ዜማ የተጀመረ ሲሆን የአንደኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ በዋናነት ገበሬን በማሞገስ ና ግብርናን በማክበር ተከብሮ ውሏል ፡፡በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ ሞትና ክረምት አይቀርምና ያለንበት የክረምት ወቅት ገበሬው በጉጉት የሚጠብቀው ፤ ዘር ዘርቶ ቡቃያ የሚያይበት፣ ቡቃያው የሚያብበት፣ አበባው ፍሬ የሚሰጥበት፣ የደረቀው የሚለመልምበት፣ የጠወለገው የሚፈካበት፣ የበጋው ወቅት ስንቅ የሚሰነቅበት፣ ተስፋ የሚጣልበት፣ የዓመት ጉርስ የሚሰበሰብበት፣ ከበሬው ጋር የሚወዳጅበት፣ ፈጣሪ ምድርን በልምላሜ የሚያስጌጥበት፣ የሚያምኑትን ገበሬዎች የሚጎበኝበት የተስፋ ወቅት መሆኑን ገልፀው ክረምቱ ገበሬ በሀገር ረሃብ እንዳይኖር፣ ሰብል እንዳያጥር ወገቡን እርፍ እየለጋው ከበሬዎቹ ጋር ሲታገል የሚቆይበት በመሆኑ ገበሬው ሊመሰገን የሚገባበት ጊዜ ነው ብለዋል ፡፡ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረ ጥቁር ማህበረሰብን ለማየትና በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነትን ታሪክ ለማድረግ ራዕይ ይዞ ሲነሳ ያለ ገበሬ ፍፁም የሚሳካ አለመሆኑን በማመን ጭምር ነው ብለዋል ፤ በመሆኑም ኩባንያው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ በተመረጡ 6 ቦታዎች ላይ በቋሚነት እንዲሁም ተንቀሳቃሽ የሆኑ 5 ሱቆችን በጥቅሉ 11 ሱቆችን ፣በአርባምንጭ ከተማ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሲከፍት ጀንበር ሳትዘልቅ የጠመደው ገበሬ ጀንበር እስክትጠልቅ ድረስ ከማሳው የማይጠፋውን ፣ እጁ ከእርፉ የማይነቃነቀውን የሀገራችንን ገበሬ በመተማመን ነውና ላቡን እያንቆረቆረ፣ ወገቡን እንዳሰረ ሲደክም የሚውለው ገበሬን ኩባንያችን ሁሌም ያከብረዋል ብለዋል ፡፡ዶ/ር ፍሰሃ አክለውም የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ባለ አክሲዮኖች ፣ የዓላማው ደጋፌዎች ፣ ሰራተኞችና ሀገራችን ኢትዮጵያን እየደቆሰ የሚገኘው የኑሮ ውድነት ችግር ታሪክ ሲሆን ማየት የምትፈልጉ ኢትዮጵያን በሙሉ እንኳን ለአንደኛ ዓመት የምስረታ በዓላችን አደረሰን ያሉ ሲሆን ሁሉም ዜጋ ገበሬን በማክበርና ለገበሬው ድጋፍ በማድረግ ቀኑን ከፐርፐዝብላክ ጋር እንዲያከብር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡በሌላ በኩል ኩባንያው ከጀመራቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶች መካከል ከገበሬው የግብርና ምርቶች መሰብሰቢያና ማከፋፈያ ማዕከል ፕሮጀክት ትውውቅ የተደረገ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብልሹ በሆነው የእሴት ሰንሰለት ምክንያት ሕዝብ እየመገበ ጾሙን ውሎ የሚያድረው ገበሬና ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ በመጣው የኑሮ ውድነት ሳቢያ ህይወቱን በትግል የሚመራው ሸማች ማኅበረሰብ እየተበራከተ መጥቷል ፤ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው የሀገራችን አርሶ አደሮች የለፍቶ አደርነታቸውን ዋጋ ሳይሆን በሥርዓቱ ውስጥ ተሰግስገው ያሉ አካላትን ኪስ ከማደለብ በተጨማሪ ውስብስብ በሆነው የእሴት ሰንሰለት ምክንያትና የዋጋ ንረት ሳቢያ ሸማቹ ማኅበረሰብ በገበያ ተደራሽነት ችግር ምክንያት ያለአግባብ የሚጠየቀው ከፍተኛ ዋጋ ማነቆ ሆንዋል። በመሆኑም ጉዳዮ ለአንድ አካል የሚተው ባለመሆኑ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ክፍተቱን ለማቃለል ከገበሬው የግብርና ምርቶች መሰብሰቢያና ማከፋፈያ ማዕከል ፕሮጀክት ሀገር አቀፍ የግብርና ምርቶች መሰብሰቢያና ማከፋፈያ መድረክን ለመመሥረት ችሏል።የከገበሬው የግብርና ምርቶች ማሰባሰቢያና ማከፋፈያ ማዕከል ፕሮጀክት ገበሬው ያመረተውን ምርት በመረከብ የሚያከፋፍልበት ፕሮጀክት ሲሆን አርሶ አደሩንና ሸማቹን ማኀበረሰብ የሥርዓቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ከማድረጉም በተጨማሪ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥርና ማኀበረሰቡን በብዙ ከሚደግፍ ልዮ ፕሮጀክት ውስጥ አንዱ መሆኑን በመርሀግብሩ ላይ ገለፃ ያደረጉት የገበሬው የግብርና ምርቶች መሰብሰቢያና ማከፋፈያ ማዕከል ፕሮጀክት ዳሬክተር አቶ አስናቀ ሀ/ሚካዔል ተናግረዋል ፡፡በመድረኩ ላይ ታዳሚዎችን የሚያሳትፍ ጥያቄና መልስ የተካሄደ ሲሆን በመርሃግብሩ ገበሬውን የሚያወድሱ ተውኔታዊ ስራዎች ፣ መጣጥፎች፣ ወጎች እንዲሁም ሌሎች የጥበብ ስራዎች ቀርበዋል ፤ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ቴሌቪዝን በቀጥታ ስርጭት በማሰራጨት በርካቶች የመርሀግብሩ ተሳታፌ እንዲሆኑ ተደርጓል ፡፡

Leave a Reply

19 − 5 =

×