ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ለህብረተሰቡ ዳቦ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑ ተነገረ።

ዋነኛ ትኩረቱን በግብርና ላይ ማለትም በእርሻ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም በሪቴል ሱቆች ግንባታ ላይ አድርጎ እየሰራ የሚገኘው ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ የግብርና ምርቶችን ከገበሬው በቀጥታ ተቀብሎ ለሸማቹ ህብረተሰብ ከማቅረብ በተጨማሪ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍም በከገበሬው መደብር አድዋ ቅርንጫፍ ላይ የማስፋፊያ ስራ እየሰራ መሆኑን እና በዛም የዳቦ፣ የጁስ እንዲሁም ሌሎች ፈጣን ምግቦች እንዲሁም መጠጦችን ለደንበኞች ለማቅረብ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ የቴክኒካል ክፍል ዋና ሀላፊ ፕ/ሮ ሽመልስ አድማሱ ለፐርፐዝብላክ ሚዲያ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ባላት ሀብት ልክ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሏን የገለፁት ሀላፊው ይህን ችግር ሊቀርፍ በሚችል መልኩ በጋሞ ዞን አርባምንጭ ከተማ በተሰጠው የ25ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ በአካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ሀይል በመጠቀም የሙዝ ቺፕስ ማምረት የሚያስችለውን ፋብሪካ እንደሚገነባም ተናግረዋል።

ሙዝ በተለምዶ ተልጦ ከሚበላው ባሻገር ለኬክ፣ ለጁስ፣ ለዱቄት እና ሌሎች በርካታ ምርቶችን እንድናመርት ስለሚያስችለን በአግባቡ ተጠቅመን ጥሩ ውጤት ልናመጣበት ይገባል ብለዋል።

ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ በተመሰረተ በ7ወር ጊዜ ውስጥ ስድስት የሪቴል ሱቆችን በአ.አ ከተማ መክፈት መቻሉ ኩባንያው በጥንካሬ እየተጓዘ ሰለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው ያሉት ፕ/ሮ ሽመልስ አድማሱ ኩባንያው ከገበሬው በቀጥታ ተቀብሎ የሚያመጣቸውን የግብርና ምርቶች ሸማቹ ህብረተሰብ በብዛት እና በቅናሽ ዋጋ በተቀላጠፈ ሁኔታ ማግኘት እንዲችል የሪቴል ዲፓርትመንት በአዲስ መልኩ መዋቀሩን ተናግረዋል።

ፕ/ር ሽመልስ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ለሚያቀርባቸው ምርቶች ደህንነት እና ጥራት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ይህን አስጠብቆ ለመጓዝ እንዲችል በእርሻ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም በሪቴል እና በሌሎች ዲፓርትመንቶች ውስጥ ለሚገኙ ሙያተኞች ኩባንያው የምግብ ደህንነት እና ጥራትን የተመለከተ ስልጠና በቅርቡ እንደሚሰጥም ይፋ አድርገዋል።

እንደ ሀገር ሁላችንም አብረን መስራት ከቻልን በጋራ ሆነን ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካን ኢኮኖሚ መቀየር ስለምንችል ይህን ሀሳብ ተጋርቶ አብሮ መስራት ለሚፈልግ ማንኛውም ተቋም ሆነ ግለሰብ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ሁሌ ዝግጁ መሆኑን ፕ/ር ሽመልስ አድማሱ አስታውቀዋል።

ናታን ታደለ
ሰኔ 25/ 2014 ዓ.ም

Leave a Reply

2 × one =

×