ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም የፐርፐዝ ብላክ ኢቲኤች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ በተገኙበት በደብረብርሀን ከተማ በሚገኙ አራት መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የምገባ ስነ ስርዓት አካሂዷል፡፡
የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሰሀ እሸቱ ዶ/ር በፕሮግራሙ ወቅት ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ከ11 ወራት በፊት በሀገራችን ላይ ያለውን የኑሮውድነት ለማረጋጋት ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረው፤ ኩባንያው የተቋቋመበት ግዜ በሀገሪቱ ውስጥ ግጭቶች የተፈጠሩበት ወቅት ቢሆንም ፐርፐዝብላክ ህብረተሰቡን ለማገልገል ካለው ቁርጠኝነት አንፃር በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቀለብ ከገበሬው በማለት ስራ መጀመሩን አስታውሰዋል::
ዋና ስራ አስፈፃሚው አክለውም ኩባንያው ከአሁን ቀደም ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የቀለብ እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ግንባር ድረስ በመሄድ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሀገራችን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ (ድርቅ)፤ በግጭት እና በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ በርካታ ወገኖች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው እንዳሳዘናቸው ገልፀው፤ ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ በሀገራችን ላይ ለሚገኙ ለእነዚሁ ተፈናቃይ ወገኖች ዘላቂ የሆነ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል #Nomorehunger የተባለው ፕሮጀክት ስራ በመጀመሩ በዕለቱ ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለተፈናቀሉ ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው የተፈናቃይ ቤተሰቦችም ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ያለማንም አስተባባሪነት ወገኖችን ለመርዳት ድጋፍ በማድረጉ አመስግነው በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ህጻናት በመሆናቸው እና ሰርቶ መብላት የማይሆንላቸው በመሆኑ በቀጣይ ይህን ችግር እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል፡፡
በመጨረሻም የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ ከፕሮግራሙ መነሻ እስከመጨረሻ ድረስ በማስተባበር ያገዙትን የማህበረ ቅዱሳን ቤተሰቦች አመስግነዋል፡፡
በህይወት ከሊል
ሰኔ11/2014 ዓ.ም
Leave a Reply