ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር አንድነት ርሃብን ለማስቆም በሚል መሪ ቃል የዓለም ታላቁ ሩጫ ውድድር ለማዘጋጀት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ አሳውቋል ፡፡መዝናኛን ለቁም ነገር ፤ አንድነት ርሃብን ለማስቆም የዓለም ታላቁ ሩጫ ውድድር እየተዝናኑ ሀገራቸውንና ህዝባቸውን በዘላቂነት መደገፍ የሚችሉብት ነውም ተብሏል ፡፡ውድድሩን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ፍ ፍሰሃ እሸቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ውድድር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በተከሰተዉ ጦርነት ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉና ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ጠባቂነት ለተዳረጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች ከመርዳት ባለፈ በዘላቂነት መደገፍ የሚችሉበት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች #ኖ ሞር ሀንገር ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው ብለዋል ፡፡በጦርነቱ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ይታወቃል ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ አቅም ያላቸው ግለሰቦች፣ ተራድኦ ድርጅቶች፣ መንግስትና የግል ተቋማት የበኩላቸውን በማድረግ በርካቶችን ለመታደግ ቢሞከርም የማስታገሻ ድጋፍ ችግሩን ጋብ ያድርገው እንጂ ከተስፋ ዳቦ ጠባቂነት ሊያላቅቅ የሚችል ባለመሆኑ በአራቱም አቅጣጫ በርካቶች መግቢያ አጥተው መንገድ ላይ ተንከራተውና ተመፅዋች ሆነው ማየት እኛ እያለን የሚያስብል ቁጭትን የሚጭር ጭምር በመሆኑ ኩባንያችን ወገኖቻችንን በዘላቂነት ሊያቋቁም የሚችል ማንኛውንም አማራጭ በመጠቀም ላይ ነው ብለዋል::በመሆኑም በ ኖ ሞር ሀንገር ፕሮጀክት ስር የሚደረገው ዓለም አቀፍ ታላቁ ሩጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፐርፐዝብላክ ራዕይን የሚደግፉና በአንድነት ርሃብን ለማስቆም የሚፈልጉ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ የሚሳተፍበት መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ዓለም አቀፍ የታላቁ ሩጫ ውድድር በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ድጋፍ የሚያደርጉ ዜጎች ሙሉ በሙሉ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረግ ነውም ተብሏል ፡፡በፐርፐዝብላክ ኢቲኤች አዘጋጅነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገውን ታላቁ ሩጫን ለዚሁ ውድድር በተዘጋጀው Great global run.com ድረ-ገፅ በመግባት ትኬት በመግዛት፣ አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ስፖንሰር በማድረግ ሁሉም ርብብር እንዲያደርግም በመድረኩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
Leave a Reply