ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር ስለ “ከገበሬው” ምርት አከፋፋይ የወጣቶች ፕሮግራም አስመልክቶ ለለሚ ኩራና ቦሌ ክፍለ-ከተማ አስፃሚ አመራሮች ገለፃ አድርጓል፡፡ ገለፃው የተደረገው በፐርፐዝብላክ ኢቲኤች የዋና መሥርያ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ገበያዉን ይቀላቀሉ እንጂ ጥቂት የሚባሉት ብቻ ተሳክቶላቸው የስራ ባለቤት እንደሚሆኑ የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ ፡፡
በልፅገዋል የተባሉ የአውሮፓ ሀገራት በእድሜ የገፋ ማህበረሰብ መብዛት ፈተና ሆኖባቸው ባለበት አለም ላይ ከአጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 71 ከመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ያሉባት ኢትዮጵያ ወጣቱ የሰው ሀይል ሲባክን ማየት የሚያስቆጭ መሆኑ የሚታበይ ሀቅ አይደለም ፡፡
በተጨማሪም ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ በስራ ላይ ከሚገኙ ጥቂት ወጣቶች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ያለ ሙያቸውና ያለ ፍላጎታቸው ስራን የሚከውኑ መሆናቸውም እንዲሁ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል ፡፡
ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ፣ ዘላቂና አስተማማኝ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ማስቻል ላይ በዋናነት ትኩረቱን አድርጎ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች የከገበሬው ምርት አከፋፋይ ወጣቶች መርሃግብር ወጣቶች ምርትን ለሸማች ማህብረሰብ እንዲያከፋፍሉ በማድረግ ለወጣቱ የተሻለ የስራ ዕድል በመፍጠር ለሸማቹ ማኅበረሰብ በመኖሪያ አካባቢው የሚፈልገውን የግብርና ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ አልሞ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ተገልጿል ፡፡
በመድረኩ ላይ ስለ ፐርፐዝብላክ ኢቲ.ኤች ገለፃ ያደረጉት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ ኩባንያው በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ የጀመረና የአባቶችን የአድዋ ገድል ለመድገም ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር ፍሰሃ አክለውም በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ፐርፐዝብላክ ኢቲ.ኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር የኑሮ ውድነትን ታሪክ እናደርጋልን በሚል መሪ ቃል ከገበሬው የተረከብነውን የግብርና ምርት በቅናሽ ዋጋ በቀጥታ ለሸማቹ በማድረሱ ረገድ ስኬታማ ሆኖ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም ምርትን ለሸማች ለማድረስ የተለያዮ አማራጮችን መዘርጋቱን ተናግረው ከገበሬው ምርት አከፋፋይ ወጣቶች አንደኛው ነው ብለዋል።
ከገበሬው ምርት አከፋፋይ ወጣቶች ፕሮግራም ወጣቶች በዘላቂነት የስራ እድል የሚፈጥር መሆኑንና ሸማቹንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች በግብርና ምርት ማቀነባበር በኢ-ኮሜርስና በችርቻሮ ሱቆች ላይ በዋናነት የትኩረት አቅጣጫውን አድርጎ እየሰራ መሆኑን የገለፁት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ዋና ቴክኒካል ኦፕሬሽንስ ኦፊሰር ፕ/ሮ ሽመልስ አድማሱ በከገበሬው ምርት አከፋፋይ ወጣቶች ፕሮግራሙ የስራ ዕድል የሚፈጥርና ታሪክ እንዲሰሩ የሚያበረታታ በመሆኑ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ወጣቶች የሸማቹን ማህበረሰብ የምርት ፍላጎት በመረዳት ትዕዛዞችን በ Kegeberew.com ድረ-ገፅ ፣ በ9858 አጭር ቁጥር ላይ በመደወልና ኩባንያችን በየወረዳው እንዲያስተባብሩ ለመደባቸው ወጣቶች በማሳወቅ ማስተላለፍ እንደሚችሉ የገለፁት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ኢ-ኮሜርስ ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል የሚገኘዉን የትርፍ ህዳግ ከ10 በመቶ እንዳይበልጥ በማድረግ ወጣቶችንና ሸማቹን ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥርዓት መሆኑንም አብራርተዋል ፡፡
Leave a Reply