ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ከልደታ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ጋር ተወያየ

የውይይት መድረኩ ”እኛ ሴቶች የኑሮ ውድነትን ለማቅለል ከመንግሥት ጎን በመቆም እንሰራለን” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን ከ500 በላይ በአነስተኛ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ተሳትፈውበታል ፡፡

በመድረኩ ላይ ከልደታ ክፍለ ከተማ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ አሰፋ ላምቦታ በኑሮ ጫና ውስጥ ሆነው የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን የሚታትሩ ሴት እህቶችና እናቶች ለሀገር ብልጽግና ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን እና እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍል መደገፍ አማራጭ የሌለውና ይደር የማይባል መሆኑን ገልጸው የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ከገበሬው ምርት አከፋፋይ ሴቶች ፕሮጀክትን አድንቀው የዕድሉ ተጠቃሚ ይሁኑ ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሀና የሺ የክረምቱ ውርጭና ዝናብ ተቋቁማችሁ ማኅበረሰቡን እየገለገላችሁ ያላችሁ በጉሊት ሥራ ላይ የተሰማራችሁ ሴቶችና እህቶቻችን ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል ፡፡

በተጨማሪም ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር በሀገርአቀፍ ደረጃ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ ያለ እናቶችና ሴቶች ሊሆን እንደማይችል በማሰብ ስላመቻቸው እድል አመስግነው ሴቶችን የዕድሉ ተጠቃሚ ሁኑ ብለዋል ፡፡

ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ከተመሠረተ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አያሌ የሚባሉ ተግባራዊ ክንውኖችን ማከናወኑን የገለጹት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ቺፍ ኦፍ ስታፍ አቶ ተፈራ ኃይሉ  ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለውለታ እናቶችና ሴቶች ከቀን ወደ ቀን ኑሯቸውን ለማሸነፍ ፀሐይ እያቀጠላቸውና በክረምት ዝናብና ብርድ እያንገላታቸው የልፋታቸውን ዋጋ የማያገኙት እናቶችና ሴቶች የጉሊት ነጋዴዎችን መደገፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተናግረው ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ያመቻቸው ከገበሬው ምርት አከፋፋይ የሴቶች ፕሮጀክት 5 ሺ ብር የሚገመት የግብርና ውጤቶችን በመረከብ ለኅብረተሰቡ እንዲሸጡ የሚያመቻች ዕድል ሲሆን በሚገኘው 10 በመቶ የትርፍ ህዳግ 5 በመቶውን ለሴቶች ቀሪውን ደግሞ ለሥራ ማስኬጃነት የሚያውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን ላይ እያገጠመን ባለው የሸቀጦች ዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር የወጣቶችን ሠርቶ የመለወጥ ተስፋ ያላሸቀና ብዙዎችን ጎዳና ላይ ያወጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የከገበሬው ምርት አከፋፋይ ሴቶች ዳይሬክተር አቶ ዳኜ ተመስገን  ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ከገበሬው ምርት አከፋፋይ ሴቶች ፕሮጀክት ለሴቶችና ለእናቶቻችን ብቻ ሳይሆን ለወጣቶችና ለመላው ማኅበረሰብ የተስፋ ጭላጭል ያሳየ መሆኑን ገልጸው በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ጋር የኑሮ ውድነት ችግራችንን እንደምንቀርፍ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት ሴት እህቶችና እናቶች መካከል ከግማሽ  በላይ የፕሮጀክቱ አባል ለመሆን መመዝገባቸውም ተነግሯል ፡፡

 

Leave a Reply

4 × three =

×