ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ከካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ጋር በሴልስ ሽያጭ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት የፈረሙት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍስሀ እሸቱ እና የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ባለቤት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኤዶም ዳምጠው ሲሆኑ፤ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ሌሎች የሁለቱም ድርጅቶቹ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ስምምነቱን ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች የሼር ሽያጩን ሙሉ በሙሉ ለካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን የሰጠበት በመሆኑ ኩባንያው ከዚህ ቀደም ካደረጋቸው ስምምነቶች የተለየ ያደርገዋል ያሉት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ፤ ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ከመደበኛ ሼር ሽያጭ በተጨማሪ በእርሻ፣ አግሮፕሮሰሲንግ አና የሪቴል ሱቆች የፍራንቻይዝ ሼር ሆልደር ሞዴል ባቀረባቸው የሼር አማራጮች ግማሽ ቢሊየን ብር የማምጣት ሀላፊነት እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ባለቤት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኤዶም ዳምጠው በበኩላቸው ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ የሰጣቸው ሀላፊነት ትልቅ በመሆኑ፤ ለዘርፉ ብቁ የሆኑ ሙያተኞችን ቀጥረው እቅዱ ውጤታማ እንዲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ነው የገለፁት።
ሀላፊዋ አክለውም ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትኩረቱን በግብርናው ዘርፍ ያደረገ ኩባንያ እንደመሆኑ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ የሚሆንበትን መንገድ ለመፍጠር ማቀዳቸውንም ነግረውናል፡፡
በሽያጭ ሙያ ከ16 ዓመት በላይ የቆየ ልምድ እንዳላቸው የሚጠቅሱት ወ/ሮ ኤዶም፤ ካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን በአሁኑ ወቅት 44 ሠራተኞችን ይዞ ከሼር ሽያጭ በተጨማሪ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ትላልቅ የንግድ ተቋማትን ማማከር እንዲሁም ለሰራተኞቻቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
አያይዘውም ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች እየሰራበት የሚገኘው የስራ መስክ በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም እምብዛም ያልተለመደ ግን ደግሞ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝበው አብሮ ከመስራት ባለፈ የኩባንያው ባለአክሲዮን መሆናቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም ወደ ፐርፐዝብላክ የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችም ከምንም በላይ ኩባንያው ያነገበውን ትልቅ ዓላማ በጥልቀት ተረድተው ሊሆን እንደሚገባ ነው ያብራሩት፡፡
ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ በአንፃሩ እንደ ፐርፐዝብላክ ፍላጎታችን በእርሻ ላይ የጀመርናቸውን ሥራዎች በማቀላጠፍ በአጭር ግዜ ፍሬያማ እንዲሆኑ ማስቻል ስለሆነ ሁላችንም በጋራ ሰርተን እቅዳችንን ከግብ ለማድረስ ቁርጠኞች ነን ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ ያመነበትን እና የሚወደውን ነገር ማከናወን ከቻለ ለስኬታማነቱ ቁልፍ ሚና አለው ያሉት የካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ባለቤት እና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ኤዶም ዳምጠው፤ በቀጣይ እንደ አንድ ድርጅት በእኔነት ስሜት ጠንክረው ሰርተው የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ከካቦድ ማርኬቲንግ ሶሉሽን ጋር ያደረገው ስምምነት ከስድስት ወር በኃላ የሚመዘገበውን ውጤት ተከትሎ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል ተገልፆል፡፡
ሪፖርተር፦ ናታን ታደለ
Leave a Reply