ፐርፐዝብላክ ኢቺኤች ትሬዲንግ አ.ማ ከFood Secured School Africa (F.S.S.A) እና ከHeritage Ethiopia Trust ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “Tree for Resilience” የተሰኘው ፕሮጀክት ሀምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ዋና ስራ አስፈፃሚው ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ የልደታ ክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ እጅጋየሁ አድማሱ እንዲሁም ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በመቅደላ አምባ 1ኛ እና 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው ይፋ የተደረገው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ በሀገራችን በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ የማስታገሻ እንጂ ከተመፅዋችነት የማያላቅቅ የተስፋ ዳቦ በመሆኑ የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች በ#ኖ ሞር ሀንገር ፕሮጀክቱ ለተፈናቀይ ወገኖቻችን ዓሳዉን ሳይሆን የዓሳዉን መረብ በመስጠት በዘላቂነት መቋቋም የሚችሉበት ስርዓት ላይ የሚሰራ መሆኑንና “Tree for Resilience” የተሰኘው ፕሮጀክትም የዚሁ አንድ አካል እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡
የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ የ#Nomorehunger ዳይሬክተር አቶ ፍሬው ክፍሌ በ “Tree for resilience” ፕሮጀክት በመጀመሪያው ዙር 1ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት 1ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አቅደን በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
እንዲህ አይነት ፕሮጀክት መጀመሩ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ለተቸገሩ ወገኖች ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለመስጠት የተሻለ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ የግሎባል ኢንቨስትመንት አማካሪ ዲማርከስ ሮስ ገልፀዋል።
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በግብርና ዘርፍ ለበርካታ አመታት ሲሰሩ እንደነበረ የጠቀሱት የግብርና ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ እስክንደር መሉጌታ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር በላይ የበርካታ ተፈጥሯዊ ሀብት ባለቤት ስለሆነች ጠንክረን በመስራት የሀገራችን ኢኮኖሚ ማሳደግ ይኖርብናል ብለዋል።
ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ድህነትን ለመቅረፍ ለጀመረው ጉዞ ምስጋናቸውን ያቀረቡት የልደታ ክ/ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ እጅጋየሁ አድማሱ በበኩላቸው መንግስት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ግብርና ተኮር የትምህርት ክፍለ ጊዜዎችን ለማካተት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረው ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች በቁጭት እየሰራ ያለበት ዘርፍ ኩሩ ትውልድ የሚፈጥር ጭምር በመሆኑ ሀሳቡን በመጋራት አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል ።
በስነ ስርዓቱ የፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሀ እሸቱ፣ የልደታ ክ/ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ እጅጋየሁ አድማሱ እና ሌሎች በመድረኩ የተገኙ የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የችግኝ ተክላ መርሀ ግብር አከናውነዋል።
ሪፖርተር ናታን ታደለ
አርታዒ ሰላማዊት ደበበ
07/11/2014
Leave a Reply