ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ በከገበሬው ምርት ስርጭት አገልግሎቱ ለተለያየ የስራ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ፡፡

ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ከገበሬው ምርት ስርጭት አገልግሎት ( KPDS ) ላይ የሚሰሩ እና ከተለያዩ ክፍለ ከተማዎች ለተውጣጡ እንዲሁም በፕሮጀክቱ በተለያየ የስራ መስክ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች ሜክሲኮ ሰንጋተራ በሚገኘው የዋና መስሪያ ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ለ4 ተከታታይ ቀናት ሥልጠና ሰጥቷል።

በሥልጠናው ላይ የፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኦፍ ስታፍ አቶ ተፈራ ሀይሉ ፣ የፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ቺፍ ኦፍ ማርኬቲንግ ዶ/ር ቴዎድሮስ እና ሌሎችም የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

መርሀግብሩን አስመልክቶ ከፐርፐዝብላክ ሚዲያ ቆይታ ያደረጉት የፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ከገበሬው ምርት ስርጭት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘካሪያስ በቀለ፤ የሥልጠናው ዋና ዓላማ በፕሮጀክቱ የሚሰማሩ ባለሙያዎችን ስለሚሠማሩበት ሥራ አጠቃላይ ግንዛቤ የተመለከተ እንዲሁም የሙያ ስነ-ምግባር እና ደንበኛ አያያዝን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩች ላይ ገለጻ መደረጉን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ ከሁለት ሺ ሁለት መቶ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው ያስረዱት ምክትል ዳይሬክተሩ፤
ይህም በሀገሪቱ ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ እየጨመረ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር ከመቀነስ አንጻር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የከገበሬው ምርት ስርጭት አገልግሎት ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት 11 ክፍለ ከተሞች ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አቶ ዘካሪያስ በቀለ ገልፀዋል።

በፕሮጀክቱ ለሚሰማሩት ሁሉም ሠራተኞች የአሰራር ስርዓት እንደተዘጋጀላቸው የገለፁት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ ባለሙያዎቹ የሸመቹን ፍላጎት ባማከለ መልኩ በየቤቱ በመሄድ ምዝገባ መጀመራቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ዘካሪያስ የከገበሬው ምርት ስርጭት አገልግሎትን ለሚጠቀሙ ሸማች ህብረተሰብ ክፍሎች የፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያን አክሲዮን በገዙት መጠን ልክ ከገበሬው ምርት ስርጭት አገልግሎት የፈልጉትን ምርት በብድር ማዘዝ እንደሚችሉ አስታወቀዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ምርትን ከገበሬው ቀጥታ እንዲደርሰው ካለበት ስፍራ ሆኖ ማዘዝ እና ጊዜውንም ሆነ ጉልበቱን መቆጠብ የሚችልበትን ይህን አጋጣሚ እንዲጠቀም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሪፖርተር፦ ህይወት ከሊል

Leave a Reply

three + eight =

×