ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም የ5000 ሄክታር መሬት ባለቤት ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ፐርፐዝብላክ ኢቲኤች ትሬዲንግ አ.ማ በፍራንቻይዝ ሼር ሆልደር ሞዴል አሁን ላይ ካለው 2200 ሄክታር የእርሻ መሬት በተጨማሪ በዘንድሮ ዓመት የ2800 ሄክታር የእርሻ መሬት ባለቤት ለመሆን አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ የኩባንያው ቺፍ ቴክኒካል ኦፕሬሼን ኦፊሰር አቶ ታደለ ሰይፉ ከፐርፐዝብላክ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

ፐርፐዝብላክ አሁን ላይ በደቡብ ኦሞ ዞን ኒያንጋቶም ወረዳ ከሚገኘው የዶግሞቴ ፋርምስ ፣ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በቆጂ ከተማ ካለው የበቆጂ እርሻ ልማት በተጨማሪ በአርባምንጭ፣ በወላይታ ሶዶ እና በባህርዳር ከተማም ሌሎች የእርሻ መሬቶች ባለቤት መሆኑን ገልፀዋል።

አቶ ታደለ አክለውም በእርሻ ፍራንቻይዝ ሼር ሆልደር ሞዴሎቹ በዶግሞቴ ፋርም እና በበቆጂ እርሻ ልማት በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ 240 ሄክታር መሬትን በጤፍ፣ በስንዴ፣ በሽንኩርት፣ በድንች እና ቃሪያ ጨምሮ በሌሎች በርካታ ምርቶች በማልማት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በቀጣይም 372 ሄክታር የሚሸፍነው የበቆጂ እርሻ ልማት በሙሉ ለማረስ እቅድ እንዳላቸው የገለፁት አቶ ታደለ በደቡብ ኦሞ ዞን ኒያንጋቶም ወረዳ በሚገኘው የዶግሞቴ እርሻ እየተመረተ የሚገኘውን 1000 ኩንታል ሽንኩርት አዲስ አበባ ከተማ በሚገኙት ሁሉም የከገበሬው መደብሮቹ እንዲሁም ኩባንያው በነደፋቸው ሌሎች ፕሮጀክቶቹ አማካኝነት ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ኩባንያው የግብርናን ምርት ከገበሬው በቀጥታ ለሸማቹ ህብረተሰብ ለማድረስ አቅዶ ወደ ሥራ ከገባ ወዲህ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳ፣ አርባምንጭ ከተማ ከሚገኙ የእርሻ መሬት ባለቤት ከሆኑ ግለሰቦች የአብረን እንስራ ጥያቄ እየቀረበለት መሆኑን ያስታወሱት ሀላፊው፤ የቀረቡትን ጥያቄዎች ከድርጅቱ ዓላማ ጋር የሚጣጣሙ ስለመሆናቸው አስፈላጊው ጥናት በባለሙያዎች በተጋዘ መልኩ በመከናወን ላይ ስለሚገኝ ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

በሸማቹ ህብረተሰብ በኩል ካለው የምርት ፍላጎት መጠን አኳያ አሁን ላይ በቂ ምርት እየቀረበ እንዳልሆነ የሚገልፁት ሀላፊው፤ በቀጣይ ጊዜያት ኩባንያው በስሩ የሚገኙትን እርሻዎች በተገቢው መንገድ በማረስ ምርት በበቂ ሁኔታ እንዲዳረስ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
እቅዱ ስኬታማ መሆን እንዲችልም ከኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር፣ ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመስራት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ታደለ፤ ኩባንያው እየሰራበት የሚገኘው የእርሻ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሚያደርጉ ስለሆነ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

Leave a Reply

2 × two =

×