ፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ደም ባንክ ጋር በመተባበር የደም ልገሳ መርሐግብር አካሄደ።
ዛሬ ሰኔ 19/2015 ዓ.ም የፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ከብሔራዊ ደም ባንክ በመጡ የህክምና ባለሞያዎች አማካኝነት በኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት በፈቃደኝነት ደም ለግሰዋል።
በመርሐግብሩ የኩባንያውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጨምሮ የኩባንያው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በፈቃደኝነት ደም የለገሱ ሲሆን ‘’በለገስነው ደም የአንድ ሰው ሕይወት ማዳን በመቻላችን ደስተኞች ነን’’ ሲሉ ስሜታቸውን አስረድተዋል።
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍስሐ እሸቱ የደም ልገሳው እንደግልም ሆነ ለኩባንያው 2ኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ፐርፐዝብላክ ለትርፍ የተቋቋመ የንግድ ድርጅት ከመሆኑም ባሻገር ከ20 ሺህ ያላነሱ ባለአክሲዮኖች እንዳሉት የሕዝብ ተቋም ደም በመለገስ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።
የብሔራዊ ደም ባንክ አገልግሎት ባልደረባ የሆኑትና ለ 93 ጊዜ ደም በመለገስ የሚታወቁት ሲስተር አሰጋሽ ጎሳ በበኩላቸው ከቀናት በፊት ለኩባንያው ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠታቸውን በማስታወስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተከሰተውን የደም ክምችት እጥረት ለመቅረፍ በሁሉም የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ዜጎች በነቂስ ወጥተው ደም በመለገስ የወገናቸውን ሕይወት ሊታደጉ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
እድሜው ከ18-68 የሆነና ክብደቱ ከ45 ኪሎ ያላነሰ ማንኛውም ሰው በ አመት ለ4 ጊዜ በየ3 ወሩ ደም መለገሥ ይችላል ያሉት ባለሙያዋ የደም ግፊት፣ የሚጥል በሽታ እና የሌሎች በሽታዎች መድሃኒት በቋሚነት የሚወስዱ ሰዎች ደም መለገስ የማይችሉ ሲሆን በፈቃደኝነት ደም ለመለገስ የሚመጣ ማንኛውም ለጋሽ አራቱን የደም ምራመራዎች ማለትም ኤች ይ ቪ፤ ሄፒታይተስ ቢ እና ሲ እንዲሁም ደግሞ የደም አይነት ልየታ በነጻ እንደሚደረግለት ተናግረዋል።
በመጨረሻም የፐርፐዝብላክ ኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች በፈቃዳቸው በለገሱት ደም በወሊድ፣ በተለያዩ አደጋና በሽታዎች ምክንያት ደም የሚፈሳቸውን ወገኖች ሕይወት ለመታደግ የሚያስችል አስተዋጽዖ በማድረጋቸው ክብር ይሰማናል ያሉ ሲሆን በቀጣይም በመሰል መርሐግብሮች በቋሚነት በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።
Leave a Reply