ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ከተማ ሼቻ የባህላዊ ምግብና ቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አስመረቀ፡፡
ፋብሪካዉ በአርባምንጭ ከተማ ሼቻ ቤሬ እድገት ቀበሌ የፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱና የዞኑ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ነዉ የተመረቀዉ
ኩባንያዉ በግብርና ምርት ማቀነባበር ዘርፍ ተሰማርቶ ለመገንባት ካቀዳቸዉ 14 ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነዉ የባህላዊ ምግብና የቅመማ ቅመም ፋብሪካ 12.7 ሚሊዮን ብር የፈጀ መሆኑም ተናግረዋል ፡፡
ፋብሪካዉ ከጅምሩ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ለ89 ሰዎች በቋሚነት ፤ 30 ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገልፅዋል ፡፡
የግብርና ማቀነባበር ተግባር ላይ የተሰማሩ የተለያዮ ኢንደስትሪዎች የግብርናን ምርት በግብዓትነት የሚጠቀሙ ከመሆናቸዉ ጋር ተዳምሮ የግብርናዉንና የኢንደስትሪዉን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል እድል ያለዉ መሆኑ ይታመናል፡፡
ነገር ግን በአግሮ ፕሮሰሲንግ ና በግብርናዉ ዘርፍ መካከል ግልፅ የሆነ የትስስር መረብ ባለመዘርጋቱና በቴክኖሎጂ ባለመደገፉ ምክንያት በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ሲቸገሩ ይስተዋላል ፡፡
ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ታዲያ ገበሬዉ ከምርት ሂደቱ አንስቶ በቴክኖሎጂ ግብዓት በመደገፍ ፣ ምርቱን ተረከቦ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እስከ ማቅረብ ብሎም የግብርና ዉጤቶችን በማቀነባበር የሚባክን ምርትን እስከ መታደግ እየወሰደ ያለዉ እርምጃ ቀደም ሲል ከነበረዉ አሰራር ልዮ ያደርገዋል ፡፡
በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ ሌሎች ከተሞች ባለታደሉት የተፈጥሮ ሀብት መገኛ በሆነችዉ አርባ ምንጭ ከተማ ላይ በርካታ ስራዎችን ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ እንዳሉ ተናግረዉ ኩባንያችን ያስመረቀዉ የባህላዊ ምግብ ማቀነባበሪያዉ ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ለመገንባት ካቀዳቸዉ 14 ፋብሪካዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡
እስካሁን ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ከ 300 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ ዕድል መፍጠሩን ገልፀው በከተማዋ የተመረቀው ፋብሪካ ለወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ አክለዉም በምድር ገነትነትዋ በምትታወቀዉ አርባ ምንጭ ከተማ ላይ በከተማዋ በስተምስራቅ በኩል የተንጣለሉ ሁለት አባያና ጫሞ ሀይቆችዋ፣ ጥቅጥቅ ያለ ደንዋ ፣ ለመጠሪያዋ ምክንያት የሆኑት 40 ምንጮችዋ፣ ከከተማዋ ጌጦች አባያና ጫሞ መካከል በግራና በቀኝ መሳለጫ “ጦሳ ዞኮ” (የእግዜር ድልድይ) ፣ የነጭ ሳር ብሄራዊ ፓርክ መገኛነትዋ ለቱሪስት መስህብነት ብቻ ሳይሆን ለልማት ጭምር መጠቀም እንደሚቻል ገልፀዉ ኩባንያዉ በቀጣይነት ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር በርካታ የልማት ስራዎችን ለመስራት በእቅድ መያዙን ገልፀዋል ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘዉዴ ለፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ዋና ስራ አስፈፃሚና ከፍተኛ አመራሮቻቸዉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈው ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች የጥቁር ህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ልህቀት ለማምጣት ይዞ የተነሳውን ሀሳብ ለማስፈፀም አርባምንጭ ከተማ ትክክለኛ ምርጫ መሆኑን ተናግረው አመስግነዋል ፡፡
የጋሞ ዞን መዲና አርባ ምንጭ ከተማ ከተፈጥሮ ሀብቶችዋ ባሻገር የበርካታ ባህላዊ እሴቶች መገኛ መሆንዋን ገልፀዉ ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች ይህንን በመረዳት በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ያሳየዉን የልማት እንቅስቃሴ አድንቀው ከቦታና ከእርሻ መሬት ማመቻቸት ጀምሮ በሚያስፈልገው ሁሉ ለማገዝ ቃል ገብተዋል ፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የግብርና፤ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የግል እና የመንግሥት አገልግሎት ዘርፎች የስራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ያላቸዉ ሚና አይነተኛ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ ያሉት የቀድሞ የጋሞ ዞን የስራ እድል ፈጠራ ልማት መምሪያ ሀላፌ የአሁኑ የጋሞ ዞን ልማት ማህበር ሀላፌ አቶ አለነ አበጀ ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች የኑሮ ዉድነትን ታሪክ እናደርጋለን በሚል መሪ ሀሳብ እየሰራ ያለዉ ስራ የሀገሪቱን ነባራዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚቀይር መሆኑን ገልጸዉ በእለቱ የተመረቀዉ የባህላዊ ምግብና ቅመማ ቅመም ፋብሪካ አምራች ለሚባለዉ የህብረተሰብ ክፍል የሚፈጥዉ የስራ እድል አይነተኛ ነዉ ብለዋል ፡፡
ፋብሪካዉ 400 ካሬ ስፍራ ላይ ማረፉን የተናገሩት የፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች አግሮ ፕሮሰሲንግ ዲፓርትመንት ሃላፌ ፐ/ሮ ሽመልስ አድማሱ 12.7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት የኢትዮጵያን ባህላዊ ምግቦችን አቀነባብሮ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲኖራቸዉ ማድረግ ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ገልጸዉ በቀጣይ 62 ሚሊዮን ብር በመመደብ የባህላዊ ምግብና ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ፕሮሰሲንግ ፋክተሪ ለማቋቋም እንደታቀደ ገልጸዋል ፡፡
ፐርፐዝ ብላክ ኢቲ.ኤች የኑሮ ዉድነትን ታሪክ ለማድረግ አብሮ በመስራት ፅንሰ ሀሳብ የተነሳ መሆኑን ተናግረዉ በመላዉ ሀገሪቱ 14 የሚሆኑ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎች በመገንባት የሚባክን የግብርና ምርትንና ፣ ጥሬ ዕቃዉን ለሌች ሀገራት በመላክ የምናባክነዉን የስራ እድል ለመታደግ የተፈጠረ ጭምር መሆኑንና በዚህም ልክ እንደ አርባ ምንጭ ከተማ ሌሎች ከተሞችም ቀና ትብብራቸዉን እንዲያሳይዮ ሲሉ ጠይቀዉ ከክልል ጀምሮ እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ ለተደረገላቸዉ ትብብር አመስግነዋል ፡፡
በመጨረሻም የጋሞ ዞን የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ተካሂዶ የፋብሪካ ጎብኝት ተከናውኗል።
በመርሃ ግብሩ ለሁነቱ መሳካት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ተቋማት እና ግለሰቦች እዉቅና ሽልማት ተሰጥቶ ተጠቃሏል፡፡
በሰላማዊት ደበበ
አርባ ምንጭ ፣ግንቦት 27 ፣ 2014
Leave a Reply